ማስታወቂያ

programs top mid size ad

የሳቅ ያለህ

“የኔ ሳቅ”
ሁሉም ለየብቻው እንደተለያየ
የኔም ሳቅ ለብቻው ከኔ ጋራ ቆየ
አየሁት ሰማሁት ሁሉን ተረዳሁት
ሳቄን ለማርከሻ ቢቸግር ጠጣሁት
ቢቸግር በላሁት
እንደ ጉሹ ጠላ እንደባር ማሽላ
ሳቄን ለማርከሻ ለነገው መድረሻ
መረጥኩት ጠራሁት
ይስቃል እንዲሉኝ ጥርሴን ተነቀስኩት
ጋዜጠኛና ገጣሚ አበራ ለማ (መቆያ)
ይህችን ወግ መፃፍ ሳስብ ትዝ ያለችኝ አጭር ግን ሀሳቤን ገላጭ ግጥም ነች፡፡ በቀጥታ ወደ ጉዳዬ ልግባ ሰሞኑን የስራ ጉዳይ ሆኖ ሳቅ ፍለጋ ‹‹የእውነት ሳቅ ፍለጋ›› የአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ዞር ዞር ብዬ ነበር፡፡ መዝናኛ ቦታ ጓደኛ ከጓደኛ ወዳጅ ከወዳጅ ሰብሰብ ብሎ የሚጫወትባቸው ቦታዎች ቦታዋቹ አሉ ያውም በደረጃና ቁጥር በዝተው፡፡ ሰብሰብ ብለው የሚጫወቱት ወዳጆችም እንደዛው፡፡
ግን እግራችሁ እስኪቀጥን ትዞራላችሁ እንጂ እውነተኛ ሳቅ አታገኙም፡፡ እንዲያው እንደግጥሟ ሰው ምን ይለኛል በሚል ፈገግ የሚል እንጂ እንደበፊቱ ሆዴን አመመኝ እስኪባል፣ የደስታ እንባ በጉንጭ ላይ እስኪወርድ የሚስቅ አታገኙም፡፡ ወይ እኔ ቦታውን አላወኩት ይሆናል፡፡
እናም ይህንን ሳይ ሰው ለምን መሳቅ አቆመ ብዬ አሠብኩኝ፡፡ ይህ ሁሉ ህዝብ ትንሽ ፈገግ እያለ ብዙውን ጊዜውን በመኮሳተር የሚወያየው ስለምን ይሆን የሚል ጥያቄ ፈጠረብኝ፡፡ እናም ላንዱ ጓደኛዬ አንተ! ሳቅ ፍለጋ ወጥቼ እውነተኛ ሳቅ አጣሁ አልኩት ትቀልዳለህ ስንት የህይወት ጥያቄ እያለብን እንዴት የእውነት እንስቃለን አለኝ፡፡
ሌላው ቀርቶ ሺህ አመት አይኖር መሳቅ ነው እንጂ ብለህ ለመሳቅ ስትነሳ እንኳን የምታውቀው ሰው ከጐንህ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ እንደበፊቱ ታክሲ ውስጥ ወይንም በመዝናኛ ቦታ ከጐንህ የተቀመጠን ሰው ነካ አድርገህ፡፡
እኔ የምልህ ብለህ ጨዋታ መጀመር አይታሠብም፡፡ያመዋል አሊያም ደግሞ ምን ሊያሶራኝ ፈልጐ ነው ብሎ ደስታህ ላይ ውሃ ነው የሚቸልስብህ ሲል ጨመረልኝ፡፡ በነገሩ ተሳሳቅን ከዛ ነገሩን ለማርዘም በሚል ለዛ ነዋ የሳቅ ትምህርት ቤት የተከፈተው አልኩት፡፡ እሱ ግን ጨዋታውን ወዲያው ቀይሮት ፊቱን ጨምደድ በማድረግ ትምህርት ስትል የትምህርት ቤት ክፍያ ስንት እንደጨመረ ታውቃለህ ብሎ ወዲያው ወደ ግል ጭንቀቱ ገባ፡፡
ለነገሩ እውነቱን ነው፡፡ የትምህርት ቤት ክፍያ ከጊዜ ጊዜ ከአቅም በላይ እየሆነ መጥቷል፡፡
ሰሞኑን እንኳን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ፣ የግል ትምህርት ተቋማት ማህበራትና የንግድ ውድድር አሠራርን የሸማቾች ጥበቃ በጋራ ሰሩት የተባለውን የጥናት ውጤት ተመልክቻለው፡፡ በዚህ ቡድን በተሠራ ጥናት ለ2007 ዓ.ም በአንድ ተማሪ የወር የትምህርት ክፍያ ላይ ከ250 እስከ 400 ብር ጭማሪ ተደርጓል፡፡
ይህ ማለት ልጁን በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምር አንድ ወላጅ በወር በአማካይ ለልጁ የትምህርት ቤት ክፍያ 724 ብር ይከፍላል ማለት ነው ታዲያ ይህ ጓደኛዬ እንዴት የእውነቱን ሊስቅ ይችላል፡፡ እናም ፈልጌ ያጣሁት እውነተኛ ደስታ እና የመጥፋቱ ምክንያቱን ከአጠገቤ አገኘሁት፡፡
ደግሞም እኮ በየመዝናኛው ቦታ ሰብሰብ ብለው ሻይ ቡና አሊያም አንድ ሁለት እያሉ የምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ እየተዝናኑ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ቀረብ ብላችሁ ብትሠሙአቸው ብዙዎቹ ውሃ ከጠፋ ወር ሆነው፣ እኔ ጋር መብራት ሳምንቱ፣ ኔትዎርክ ቢሆንስ የታለ የሚል ጨዋታ ነው የምትሠሙት፡፡ አንድ ወደ ቤቱ ገብቶ ልጁን ሊያስጠና የጓጓ አባት ከቢሮ ወጥቶ ወደቤት ልሂድ ብሎ ልጄ መጣሁልሽ ብሎ ሲደውል መብራት እኮ የለም ብላው በዚህ ንዴት ቢጠጣ እስኪመጣ ብሎ አንዱ ጋር አረፍ ቢል እንዴት ሊዝናና ይችላል፡፡
ወይም አንድ ሁለት ብሎ እና ተሠናብቶ በጊዜ ከቤቱ ሊገባ የፈለገ አባወራ ሚስቱ ጋር ደውሎ “ውዴ መጣው” ሲላት ጨለማነው ሻማ እንዳትረሳ ብትለው ቅስሙ ስብር ብሎ እንዴት ከዚህ ሰው ጨዋታ እና ሳቅ ይጠበቃል፡፡
ወይንም ጠዋት ከቤቱ ሲወጣ ውሃ ዛሬም ስላልመጣች የታሸገ ውሃ ይዘህ መምጣትህን እንዳትዘነጋ አሊያም ያንን ልብስ አስጡኝ ብትሉ ቤትኛው ውሃ ይታጠብ እንደቆሸሸ ነው ቢባሉ ከዚያ በኋላ እንዴት በደስታ ቀኖትን ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡
ከሰኞ እስከ አርብ ሰራን ነገንማ አብረን ዘና ብለን ነው የምናሳልፈው ብለው የተቀጣጠሩ ኩብሎች በነገታው ዝንጥ ጥንቅቅ ብለው ወጥተው በኔትዎርክ ምክንያት ሳይገናኙ ቢቀሩ ደስታቸው እንዴት ደስታ ሊሆን ይችላል፡፡
አንዱ ጋር አረፍ ብዬ ቆንጆ ሙዚቃ ልስማ ብሎ ከቤት የወጣ ሰው ካሰበበት ቦታ ደርሶ ነብሱ የጠየቀችውን ሊሞላ ገና አረፍ ሲል መብራት ድርግም ብሎ በቦታው ጄኔሬተር መንደቅደቅ ሲጀምር እንዴት ብስጭት እንደሚያደርግ አስቡት ከዚህ በኋላ ደስታውስ እንዴት ደስታ ሊሆን ይችላል፡፡
ኳስ እንኴን እያየን እንደሰት ብለን ከቤት ብንወጣ የኔን ቡድን ለምን አልደገፍክም እኔ የምደግፈው ቡድን ገብቶበት ጆሮዬ ላይ በደስታ መጮህ አትችልም ምናምን ተብለህ ኩምሽሽ እድትል ትደረጋለህ፡፡ ያውም ዱላም ካልቀመስክ ተመስገን ነው፡፡ ብቻ ሌላም ብዙ እንዳንደሰት “የእውነት” እንዳንስቅ” የሚያደርጉ ሀሳቦች ማንሳት ይቻላል እያለ ይህ ጓደኛዬ የሆነውን ፣ የሰማውንና የጠረጠረውን እያጫወተኝ ብዙ ከቆየን በኋላ ካለንበት አካባቢ በህብረት የተጮኽ ጩኽት ከቀለጠው ውይይታችን መለሰን ምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ መብራት ጠፍቶ ነበር ሲመጣ ደስ ብሎአቸው ነው የጮሁት ተባልን፡፡ ይህን ስሰማ በአንድ ወቅት የመብራት መቆራረጥን በተመለከተ ከነዋሪዎች አስተያየት ስጠይቅ አንድ ወጣት ያለኝ ትዝ አለኝ ፡፡ ወጣቱ እኔ እኮ ይገርመኛ ሲጠፋ ፀጥ ፤ ሲበራ ኡኡ እንላለን መብታችን የምንከፍልበት አገልግሎት ነው፡፡ ስንነጠቅ ወይንስ ሲመለስልን ነው መጮህ ያለብን ነበር ያለው፡፡
 
ቁልፍ ቃላት
Fri, 08/01/2014 - 07:24