ማስታወቂያ

programs top mid size ad

በነካ እጃችን ይቅር እንባባል

ሳምንቱ እንዴት አለፈ? መቼም የሳምንቱ ትልቁ ወሬ ምን ነበር ተብሎ ቢጠየቅ የምንበዛው እንዴ ይቅርታ መባላችን ነዋ! ያውም በፕሬዝዳንታችን የምንል ይመስለኛል፡፡ ለኔ በግሌ የሳምንቱ ብቻ ሳይሆን ያለመድኩት ስለሆነ ከማረሳቸው ቀኖች ውስጥ አንዱ ነው ብዬ ለመናገር እችላለው፡፡ ይህ ማለት ግን ይቅርታውን ብቀበልም ሌላ ጥያቄ የለኝም ማለት አይደለም፡፡ ባለፈው ሳምንት ፓርላማው ስራ ሲጀምር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በመብራት መቆራረጥ ለገጠማችሁ መንገላታት ይቅርታ እንጠይቃለን አሉን፡፡ ይቅርታው በጣም የዘገየ ቢሆንም አንዳንዶቻችን መብራት ጠፍቶብን መረጃውን በስልካችን ሬዲዬ ሰምተን ይቅርታውን ተቀብለናል አልን፡፡ ለማንኛውም ግን ይቅርታ መባባሉን መልመዳቸን መልካም ነገር በዘመኗ አማርኛ ደግሞ ‹‹ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ›› ቢሆንም ይቅርታውን የበለጠ አስደሳች ለማድረግ በስራው ውስጥ ያሉት ማድረግ ያለባቸውን ማድረግ ጥፋት ሠርተው ከሆነም እነሱም ይቅርታ ማለት አለባቸው፡፡ በይቅርታው ወቅት፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እስኪጠናቀቁ በትእግስት መጠበቅ እንዳለብን ተነግሮናል፡፡ ይሄ የግድ ነውና ብዙዎቻችን የምንቀበለው ይመስለኛል፡፡

ግን እነዚህ ሲጠፋ በቶሎ አይመጡም የሚባሉት ሰውን ጨለማ ውስጥ አስቀምጠው በገንዘብ ይደራደራሉ እየተባሉ የሚታሙት አንዳንድ የመብራት ሀይል ሠራተኞችንና ደውሉ ብለው ስልክ እየሠጡን በችግር ጊዜ ስንደውል የማያነሱትን ሠራተኞች እስከ መቼ ነው የምንታገሳቸው፡፡ እነሱም በመሠራት ላይ ነው እንደተባለው ፕሮጀክት በሂደት ነው እንዴ ግዴታቸውን እያወቁ የሚመጡት፡፡ ለማንኛውም እነሱም ይቅርታ ብለው ከቸግራቸው ከታረሙ ይቅርታው የበለጠ ያማረ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጪ ይቅርታው ለምን ለመብራት ብቻ ሆነ የሚል ጥያቄንም የባለፈው የይቅርታ ቃል ፈጥሮብኛል፡፡ 
ለነገሩ ለሁሉም ስህተትና ጥፋት ፕሬዝዳንታችን ይቅርታ ይጠይቁን ብሎ ማሰብ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ግን ልክ እንደ መብራቱ ሁሉ ይቅርታ ይህ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው ሳይሉን እንደገዛ ንብረታቸው ብዙ ነገር ያጠፉብንና ያጐደሉብንም በነካ እጅ ይህቺን የተሟሟቀች የይቅርታ ጊዜ ተጠቅመው ይቅርታ ቢሉን እኛም አፉ ብንላቸው መልካም ይመስለኛል፡፡
ውሃና ፍሳሽ፣ ፈረቃ ተጀምሯል ሳይለን በዚህ ሰዓት ይጠፋል ብሎ ሳይነግረን ለቀኖች እና ሳምንታት ውሃን የውሃ ሽታ እያደረገብን አይደለም እንዴ ይህን ችግር ሊፈታልን እስከዚህ ጊዜም እንዲህ አደርጋለው እስካሁን ለሆነውም ይቅርታ ሊለን አይገባም እንዴ? የአዲስ አበባ የማስፋፊያ ስራን ጨርሻለው ካለ በኋላ ጩህቱ ትንሽ ጋብ ቢልለትም አሁንም ግን ጥያቄ የሚነሳበት ለኛ አገልግሎቱ እምቢ እያለን እሱ ግን በቀን አስር ጊዜ የምንፈልገውንም የማንፈልገውንም መልዕክት በተንቀሳቃሽ ስልካችን እየላከብን የሚያሠለቸን ኢትዮ ቴሌኮምስ ይቅርታ ሊለን አይገባም እንዴ? በየቀኑ የማይልክልን የአጭር የመልዕክት አይነት የለም ፊት ለፊት ይቅርታ ማለቱ ቢቀር ከሚመጡት አጭር መልዕክቶች ቢያንስ አንዱ ይህ የሆነው ይህ ስለተፈጠረ ነው ታገሱ ለአገልግሎቱ መስተጓጐል ግን ይቅርታ የምትል አጭር መልዕክት ለልክልን አይገባም እንዴ?
ሌላም ማንሳት ይቻላል በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየደረሱ ካሉ የትራፊክ አደጋዎች የሚበዛውን የሚያደርሱት አዲሱን የመረጃ ፈቃድ የያዙት ናቸው ሲባል ይሠማል፡፡ ተሸከርካሪን ከመሳፈር ያለፈ ቀረቤታ ለሌለው ሰው ሁሉ ክፈል እንጂ ያሻህን በአንዴ ውሠድ 4ኛ ይሻልሀል 5ተኛ እያልን መስጠታችን ለዚህ ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ጥናትም ጭምር አረጋግጦታል እየተባለ ሲነገር ደጋግመን ሠምተናል፡፡
በዚህ ምክንያት ብዙ ህይወት ጠፍቷል፣ አካል ጐሏል፣ ቤተሰብ ተበትኗል፣ ንብረትም ተበትኗል፡፡ ግን ይህ ስህተት ነበር ይቅርታ የምንባለው መቼ ነው?
ለኛ ሀገር የማይሆኑና የማይመጥኑ ናቸው እየተባሉ በተደጋጋሚ ስማቸው የሚነሳ ተሽከርካሪዎችስ በእውነትም ለኛ የማይሆኑ ስለመሆናቸው በተጨማሪ በባለሙያ የሚጣራ ቢሆንም ግን ቢያንስ ለማጣራት ፍላጐት እንኳን የምናሳየው መቼ ነው? ከጠፋስ መፍትሔ የምንፈልገው ለጥፋቱም ይቅርታ የምንጠየቀውስ መቼ ነው?
በህክምናውም በባለሙያና በህክምና ተቋም ስህተት ስንት ጥፋት ሲደርስ ስንሠማና ስናይ ከርመናል የሚበዙት ሞያና ግዴታቸውን አክብረው ቢሠሩም ጥቂቶች ደግሞ ይህንን ክቡር ሞያ ሲያረክሱ አይተናል ሠምተናል፡፡ የጠፋውን የምናርመው እስካሁን ለሆነውስ ይቅርታ የምንጠየቀው መቼ ነው?
መንገዶቻችን በተገቢው መንገድ የተሠሩ እንዳሉ ሁሉ በተለያየ ጥቅም ሰበብ የውሸት የተሰሩም ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለመንገዶቻችን ሳስብ አንድ ወቅት ስለዚሁ የመንገድ ስራ ችግር ውይይት ሲደረግ አንድ በሙያው ሰርቬየር ነኝ ያለ ሰው በስልክ ገብቶ የሠጠውን አስተያየት አስታውሳለው፡፡

ሰውዬው ለመንገድ ስራ የሄደበት አንድ የገጠር መንገድ ፕሮጀክት በጊዜው ሳይገባደድ ይቀርና አንድ ዝግጅት ሊደረግ ታስቦ እግረ መንገዱን ያ መንገድም ይመረቃል፣ ባለስልጣኖች ይመጣሉ በቶሎ ይለቅ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ተሠጠ፡፡ አመናችሁም አላመናችሁም በወጉ ከስር ንጣፍ እንኳን ሳይደረግ የተጠረገው መንገድ ላይ አስፋልት እንዲለብስ ተደረገ ነበር ሲል የሠማሁት፡፡
ለማንኛውም በመንገድ ጉዳይ የተሠሙ የተለያዩ አስገራሚም አሳዛኝም ታሪኮች ተሠምተዋል፡፡ ግን ለዚህ ሁሉ ችግር ጥፋት መሆኑ ከታወቀ ይቅር መባል የለብንም እንዴ?
በሌላውም በየመስሪያ ቤቱ ለተለያዩ ጥቅም በሚል ስልጣን ማገልገያ መሆኑን እረስተው እርስት የሚመስላቸውና በህዝብ ላይ ስንት እንግልት የሚያደርሱ መቼ ነው ከጥፋታቸው የሚታረሙት? ለሠሩት ጥፋትስ ይቅርታ የሚሉን?
ለማንኛውም በነካ እጃችን በዚው አጋጣሚ ከአንገታችን ሰበር ብለን ይቅርታ ብንባባል ከጥፋታችን ብንታረም መልካም ነው፡፡ ታዲያ ከልብ መሆን አለበት፡፡
ቁልፍ ቃላት
Tue, 10/14/2014 - 08:19