ማስታወቂያ

programs top mid size ad

መቆየት ወይስ ታሪክ ማቆየት?

በኢትዮጵያ እና በኢጣሊያ መካከል ስለተወደረገው ጦርነት ስታስቡ መጀመሪያ ወደ አእምሯችሁ የሚመጣው በቪዲዮ ምስል የትኛው ነው? ወይም በየአመቱ የአርበኞች መታሰቢያ ወይም የአድዋ ድል መታሰቢያ ቀን ሲከበር ተደጋግሞ ለቴሌቪዥን ዘገባ ጥቅም ላይ የሚውል ባለ ነጭ እና ጥቁር ተንቀሳቃሽ ምስል? በእርግጠኝነት የጦር መሪዎች ፈረስ ላይ ተቀምጠው፣ወንዶች ጦር እና ጋሻ ይዘው፣ሴቶች አገልግል ተሸክመው ሲፎክሩ እና ሲሸልሉ ያያችሁት ይሆናል፡፡በርካታ ሰዎች ታሪኩ በተከሰተበት ወቅት የተቀረፀ የሚመስላቸው ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ የተሠረተችበት 100ኛ ዓመት በዓል በ1979 ዓ.ም ሲከበር ለበዓሉ ድምቀት ሲባል በድጋሚ መልሶ የተከወነ ነው፡፡ የታወቁ ተዋንያንን ጨምሮ ወደ 4000 ሰዎች እንደተሳተፉበት ይነገራል፡፡ ምስሉ በታዋቂው የቲያትር ዳይሬክተር አባተ መኩሪያ የተዘጋጀ አድዋ ድልድይ በሚባለው እና አሁን ላይ በዘመናዊ አስፋልት በተሸፈነው ሜዳ ላይ የተቀረፀ ነው፡፡ ድራማዊ የምስል ቀረፃው የከተማ ልደትን ለማክበር የታሰብ ብቻ ሳይሆን ታሪክን ለማቆየት የተደረገ ሙከራም ነበር፡፡

ይህ ጨዋታ ያለ ነገር አልተነሳም፡፡ ከተማችን አዲስ አበባ በፈጣን የለውጥ ሂደት ላይ ትገኛለች; በከፍተኛ የመልክ ወይም የገፅታ ለውጥ፡፡ ከጠባብ እና ኮሮኮንቻማ መንገድ ወደሰፋፊ አስፋልት እና ኮብል ስቶን ንጣፍ መንገድ፣ካዘመሙ የጭቃ መኖሪያ ቤቶች ባለድርብርብ ፎቅ ዘመናዊ ህንፃዎች፤እርስ በርስ ከተዛዘሉ እና ጣራቸው በሮ እንዳይሄድ በድንጋይ ከተጠበቁ ደሳሳ ጎጆዎች በስነህንፃ ውበታቸው ያማሩ፣የተራቀቁ፣ በመስተዋት ያሸበረቁ ሆቴሎች እና የገበያ ማዕከላት፣የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፣የቀለበት መንገድ፣የቀላል ባቡር መንገዶች፡፡ አዲስ አበባ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት የነበራት ገፅታ እና ከ10 ዓመታት በኋላ የሚኖራትን መልክ ሁለት የተለያዩ ከተሞችን የማነፃፀር ያህል ሊከብደን ይችላል፡፡

በነገራችን ላይ ይህ ወግ የአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የከተማቸውን ገፅታ ለመቀየር በሚሞክሩ የአፍሪካ ሀገራትም ያለ ነው፡፡ በናይሮቢ(ኬኒያ) እንዲሁም በሌጎስ(ናይጄሪያ) ተመሳሳይ የከተማ ዕድገት ስራ አለ፡፡ ለአመታት የኖሩ የድሆች መኖሪያ ሰፈሮች ለአዳዲስ ህንጻዎች እና ባለሀብቶች ቦታቸውን ለቀዋል፡፡ በአውሮፓ፣ በአሜሪካም በተለያየ ጊዜ ከተሞች በከፊል ወይም በሙሉ መልካቸውን ቀይረዋል፡፡ እነዚህ መልካቸውን መለወጥ የፈለጉ ሀገራት የከተሞቻቸውን ገፅታ ለውጥ በፎቶ እና በቪዲዮ ቀርፀው ያስቀምጣሉ ብለን ተስፋ እናድርግ(እገሊት የተባለችው ከተማ/ሠፈር ድሮ እና ዘንድሮ ዓይነት ነገር)፡፡ልክ ማንኛውም ሰው ህፃን እያለሁ፣አድጌ፣ ከከፍተኛ ትምህርት ስመረቅ፣ሳገባ፣ስወልድ እያለ የገዛ ታሪኩን አቅሙ እና ዕውቀቱ በፈቀደው ቴክኖሎጂ እንደሚያቆየው፡፡

ለምሳሌ ያህል አንድ ፊልም ሰሪ በ1960ዎቹ፣ ወይም 70ዎቹ፣90ዎቹ - - - ኧረ ምን ሩቅ አስኬደን? 2005 ዓ.ም ላይ አዲስ አበባ ላይ የተከናወነ ታሪክ መስራት ፈለገ፡፡ ታዲያ አሁን ባለችው አዲስ አበባ ላይ ልስራ ቢል ይችላል? የድሮዋን አዲስ አበባ አስመስሎ ይሰራል?መቼም በአድዋ ጦርነት ወቅት የነበረውን ሜዳ ለማምጣት የሚቀለውን ያህል አይቀልም፡፡ ፊልሙ ቀርቶ እስኪ ለማሰብ ያህል አሁን ላይ ቆመው በፊት ያውቁት የነረውን የአዲስ አበባ መንደር እና መንገድ በምናብዎ ለማስታወስ ይሞክሩ? አሁን ያማረ የቀለበት መንገድ ያረፈበትን የጎተራ መንገድ፣የባቡር መንገድ የተዘረጋበትን መስቀል አደባባይ፣በታላላቅ ሆቴሎች እና ህንፃዎች የተቀየረውን የካዛንቺስ ሠፈር፣ልደታ፣የአራት ኪሎዎቹ እሪ በከንቱ እና ባሻወልዴ ችሎት፣ውቤ በረሀ፣መሿለኪያ፣ሜክሲኮ - - -፡፡ ሜክሲኮ አደባባይ ትዝ ይላችኋል? ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በሊግ ኦፍ ኔሽን የሀገራት ማህበር ስብሰባ ላይ ኤርትራን ከእናት ሀገሯ ለመቀላቀል ስትሟገት ድጋፍ ለሰጠቻት ብቸኛ ሀገር ውለታ የተቀመጠ መሪ ሀውልት? የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት፡፡ በነገራችን ላይ ከባቡር መንገድ ስራው በኋላ ወደቀድሞ ቦታው እንደሚመለስ የሚነገረው የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ለ3ኛ ጊዜ እንደሚቆም ታውቃላችሁ? ሁለቱን ያቆሙት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የተሰራው ሀውልት የሮማ ጳጳስ እንጂ ኢትዮጵያዊ አላስመሰላቸው ተብሎ የማሻሻያ ሀውልት ተሰራላቸው፡፡ ሁለተኛው ሀውልት ላይ የተገደሉበትን መሣሪያ የሚወክል መትረየስ፣ የጳጳስ ቆብ ፤ እጃቸው የታሰረበት ሰንሰለት ተካቷል፡፡(የመጀመሪያው ሀውልት እሳት አደጋ መከላከያ የሚባለው ጊቢ ተቀምጦ ከኖረ በኋላ በ1982 ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጊቢ ውስጥ ሚዩዚየም ሲሰራ ወደዛ ተዛውሯል፡፡ ታሪኩን ከፈለጋችሁ ሙዚየሙን ጎብኙ፡፡) ይሄው ሀውልት ለ3ኛ ጊዜ ሲቀመጥ ቢያንስ የአቀማመጥ እና በአካባቢው ላይም ለውጥ መኖሩ አይቀርም፡፡

የከተማችን ዕድገት ለውጥ በዲዛይን፣ ወይም በማንኛውም ዲጂታል መሳሪያ ተዘግቦ እየተቀመጠ ነው፡፡ ከአመታት በኋላ የቀድሞዋን አዲስ አበባ ከተማ ገፅታ የምናይበት ሚዩዚየም፣ወይ ቋሚ ኤግዚቢሽን ወይ የሆነ ታሪክ ይኖረናል? ለመዝናኛ፣ለጥናትና ምርምር እንደው ለታሪክ ያህል ታሪክ ይኖረናል? ክፍል ሁለት የ‹ወፌ ቆመች› ድራማ በዚሁ ታሪክን የማቆየት ጉዳይ ያወራል፡፡ አወራሩ ግን ሰዋዊ የሆነ ገፅታ አለው፡፡ የድራማው ባለታሪኮች ለልማት በመነሳት ላይ ያለውን ‹የሞጃ ሰፈራቸው›ን ታሪክ ለማቆየት አስበዋል፡፡ እስኪ ድራማውን አዳምጡትና በጉዳዩ ላይ ያለዎትን አመለካከት ያካፍሉን፡፡
ቁልፍ ቃላት
Sat, 12/27/2014 - 09:17