ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ለምን ግን አንሰለፈም

በአለም ከጫፍ እስከ ጥግ በኑሮ ውጣ ወረድ በየሁሉም ማዕዘን የፈለጉትን ለማግኘት የታለመውን ለመፍታት ከታሰበው ለመድረስ በየሁሉም መንገድ ችግሮች እንደ አሽን የበዙ ናቸው፡፡ መሰናክሎችን መዝለል እና ማለፍ ይደክማል ፈተናዎችንም መቁጠር ይታክታል፡፡ ታዲያ በዚ ሁሉ መመላለስ ግን ችግሮችን ለመፍታት ከማሰብ ይልቅ ለእክሎቹ መፍትሄ የሚሆኑ ሃሣቦችን ከመምዘዝ ውጪ እና የተፈጠሩትን ችግሮች በትዕግስት ጠብቆ ከመፍታት ባሻገር ባልተገባ አቋራጭ እና በተሰባሪ ድልድይ ላይ ለማለፍ መሞከር የእክሎችን ጐዳና ከማርዘም ውጪ አና የባሰ ዝፍቀት ውስጥ ከመክተት ባሻገር ትክክለኛ አማራጭ ሆኖ አይታይም፡፡ ታዲያ ችግሮችን ለማቅለል እስከጭራሹም ለመፍታት በግለሰብም ይሁን በማህበር በሀገርም ይሁን በአለም ደረጃ በሚደረጉ እቅንስቃሴዎች ሁሉ ሁሉም ግቡን አንድ እያለ ለማስቆጠር ችግሮችን ለመፍታት ተራው ደርሶ ከእልፍኝ ለመግባት የተፈለገው ላይ ለመድረስ መሰለፍ እንደአማራጭ ሳይሆን ግዴታ ይሆናል፡፡ ለምሣሌ በኑሮ ውጣ ወረድ ውስጥ አብዛኛው ማህበረሰብ የትራንስፖርት ተጠቃሚ ነው የታክሲ ፡ የአውቶብስና ሌላም ሊሆን ይችላል ፤ በማለዳ ሁሉም እንደደረጃው እንጀራውን እና የዕለት ጉርሱን ለማብሰል እንደየፊናው ተሰልፎ ጊዜ ቆጥሮ ባገኘው እና በተካነበት ሙያ ለመሰማራት ዕለቱን ሀ ብሎ ለመጀመር ወደ ሚሰራበት ያቀናል፡፡ወደ ሥራ ቦታ ለመሄድ የታክሲ አገልግሎት መጠቀም የሚፈልግ ይኖራል ፤ በህይወት ውስጥ ብዙ የምንሰለፍባቸው ሰልፎች እንዳሉ ሆኖ የታክሲ ሰልፍም አንዱ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እዚህ ጋር ካሰቡት ለመድረስ የተሰለፉት የታክሲ ላይ ሰልፍ ረዘሞ የታየው ከኋላ ሄዶ ላለመሰለፍ ከመሀል ጓደኛ ይፈልጋል የሚያውቀው ሰው አሊያም ከመሀል ነበርኩኝ ብሎ ግብግብ ይፈጥራል፡፡ የለም አትገባም ከኋላ ሂድ እና ተሰለፍ የሚለው እንደክፉ ይታያል እንደባለጌ ማነው ክፉ? ማነው ስርዓት የናደ? መሥሪያቤት ሂዱ በአንድ መሥራያ ቤት ውስጥ ደረጃ ወይም እድገት ማግኘት ያለበት ሰራተኛ በርትቶ እየሰራ እና የሚያስፈልገው ሰልፍ ላይ ተገኝቶ እያለ በአቋራጭ ከቅርብ አላቃ ጋር በዝምድናም ይሁን በሌላ ስህተት መንገድ ዕድገቱ ላልተሰለፈው ይሰጣል፡፡ ወደ ሆስፒታል ደግሞ ልውሰዳችሁ ጤናውን ያጣ አልያም የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ካርድ ለማውጣት የተሰለፈው እያለ በስልክም ይሁን በሆስፒታል ውስጥ የሚያውቀው ሰው ስላለ ካርድ ያገኛል ፤ ቅድሚያ ይሰጠዋል ህመሙ የበረታባቸው ደግሞ አልጋ ለማግኘት ተሰልፈው ላልተሰለፉ ህመምተኞች እና በሆስፒታሉ ዘመድ ላላቸው ባዶ አልጋ እያለ አይ የለም አልጋ አልቋል ይባላል፡፡ ይሄስ እንዴት ይታያል? ወደ መሥሪያ ቤት ደግሞ ተመልከቱ አንድ መሥሪያ ቤት ማስታወቂያ ያወጣል አብሮኝ የሚሰራ እፈልጋለው ብሎ ግን የስራ ልምዳቸውን እና የትምህርት ደረጃቸውን የሚያሟሉ የተሰለፉ እና በበሩ መግባት ያለባቸው እያሉ ከውስጥ ሰው ጋር ስለሚተዋወቁ ብቻ ውድድር ሳያደርጉ እና ሳይፎካከሩ በመስኮት ዘለው እና ዘው ብለው የሚገቡ ብዙ አሉ፡፡
ታዲያ ዞሮ ዞሮ በተሰባሪ ድልድይ ላይ መጓዝ አለመሰለፍ የሀገር ችግር አይሆንም ትላላችሁ ፤ እዚ ጋርስ የስብዕና ጉዳይ ሲወደድም አይሰማችሁም፡፡ ሰሞኑን እንኳን ተፈጥሮ በነበረው የነዳጅ እጥረት ወይም አለመኖር ምክንያት ብዙ መኪኖች በየማደያው ተሰልፈው አይተናል ተራ ይደርሰኛል ብለው አንድ ሰዓትም ይሁን ከዚያ በላይ የቆሙ ሰልፈኞች እያሉ እነሱም ስራቸውን ትተው እንጀራ ሆኖባቸው ሌላው ስራ አለኝ ባይ ከተሰለፉት መኪኖች ኋላ ሄዶ መሰለፍ ሲኖርበት ከኋላ ላለመሰለፍ ደርቦ ሰልፉን ሲረብሽ ሲጋጭ እና ማደያዎችም በፀጥታ አስከባሪዎች ሲታገዙ ነበር! ሰልፍን ለማስተማር መሆኑ ነው፡፡ ሰልፍን መማር ያለብንስ አሁን ነው፡፡ ይህን እንደ ምሣሌ አነሳን እንጂ ሰልፍ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡ በህይወታችን ብዙ የምንጠይቃቸው ፣ የምንፈልጋቸው እና የሚያስፈልጉንን ነገር ለማግኘት ሂደቶች ያስፈልጉታል መሰለፍ ማለቴ! ደንቦችን ለማውጣት እና አዋጆችን ለማፅደቅም በሚደረገው የሀሳብ ልውውጥ አንዱ ከአንዱ እየተደማመጠ ሀሳቡን ለመናገር ተራውን ጠብቆ ተሰልፎ ያመነበትን ሀሳብ ለመሰንዘር ካልተጠባበቀ በሀሳብ ላይ ሀሳብ ይሆናል፡፡ መደማመጡ ቀርቶ ካልተፈለገ ድምዳሜ ላይ ይደረሳል ይኸ እንዳይሆን ሃሣብንም ለመናገር መሰለፍ ባይዘነጋ መልካም ነው፡፡ በሰልፍ መደዳ የተሰለፈው ተራው ደርሶ የሚፈልገውን ያገኛል በህይወት ውስጥ ያጋጠሙትን ችግሮች ታግሶ ያልፋል፡፡ አንድ ቀን ይሆንልኛል ይሰምርልኛል ብሎ በማሰብ ብርድ ሳይበግረው ፀሐይ ሳይሰለቸው የሰልፍ ርዝማኔ ምንም እንኳ አሰልቺ ሆኖ ጉልበት ቢዝልም ባጠቃላይ የታሰበው ላይ ለመድረስ ይሰለፋል! በተመሳሳዩ በአቋራጭ ለመክበር ያልሰሩበትን ለማፈስ አና ወደ ኪስ ለማድረግ ያለ ስርዓት በሰው ሰልፍ እየገቡ ሰልፉን የመናድ አቅም ያላቸው ግን ስብዕና የጐደላቸው በጥበብ በንግዱ በስልጣን በአጠቃላይ የህይወትን ሰለፍ ሳይሰለፉ ሰልፉን የሚያወናብዱ የሰልፍ አወናባጆች አሉ፡፡ በአቋራጭ መክበር ፣ በአቋራጭ እንደሚጥል ያልገባቸው ቢሰለፉ መልካም ይሆናል፡፡ ሰልፉ ታዲያ የቅንነት ማድጋቸው ተንጠፍጥፎ ላለቀባቸው የማስተዋል እና የበጐነት መሶባቸው ቢከፈት ባዶ ለሆነባቸው የለጋስነት እና የቸርነት እጆቻቸው ላጠረባቸው እና በነዚ ጐዳና ላልተሰለፉ የስልፍ ርዝማኔ ምን ለዓይን ቢደክም ሀሞትን አፍስሶ የማይገፋ ሆኖ ቢመስልም አንድ ቀን ከታሰበው ይደርሳል እና እንሰለፍ!
ቁልፍ ቃላት
Fri, 01/02/2015 - 08:53